ታላቋ ሮማ ስለምን ወደቀች?

ሮማየታላቋ ሮማ ታላቅነት የሚጀምረው ሪፐብሊኩን ከገነቡት ከሮማ ሰዎች ጥንካሬ፥ ፅናት፥ ቆራጥነት፥ ጠንካራ ሰራተኝነት፥ ራስን ለመቻል ካላቸው ፅኑ ፍላጎት፥የሰው የሆነን ነገር ከመንጠቅ ቁጥብ መሆናቸው ወዘተ በተላበሱት ባህሪያቸው ላይ ነው። አዎ! በርግጥ እነዚህ የሮማዊያን መገለጫዎች ጥንት እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም የሰው ልጅ የነፃነት ምሰሶዎች ናቸው። ታላቋ ሮማ በነዚህ ታላላቅ የሰው ልጅ መልካም ባህሪያት የታነፃች ነበረች።

ሮማዎች የመጀመሪያውን ሪፑብሊክ ሲመሰርቱ እንደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት ግብርና ነበር። የአብዛኛው ህዝቧ ኑሮም ከእርሻ እና ግብርና ጋር የተሳሰረ ነው። ቀስ በቀስ የገጠር ከተማዎቿ እየተለወጡ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እና የገበያ ትስስሮች እየጠበቁ በጠንካራ የህግ ስርዓት ላይ ተመርኩዘው መስፋፋት ያዙ። ጥንታዊት ሮም ኢኮኖሚዋን ነፃ ማድረጓ፥ ለመንግስት ስልጣን በህግ ልጓም ማበጀቷ፥ ለኢንተርፕርነሮች፥የፈጠራ ውጤት ባለቤቶች እንዲሁም ማንኛውም ሰው የሚያፈራውን ሃብት ከቀማኛ የሚጠብቅ ጠንካራ የህግ እና የፍትህ ስርዓት መመስረት መቻሏ ዋነኛ የእድገት መሰላል ሆነዋታል። ማደግ መመንደግ በጀመረው የሮማ ኢኮኖሚ የተማረኩ በርካታ የሌላ ሃገር ሰዎች ስራ ፍለጋ ወደ ሮማ ማቅናት ያዙ።

የሮማዊያኑ የንፅህና አጠባበቅ፥ የትምህርት አሰጣጥ፥የባንክ ስራ ፥የግንባታ እና የንግድ አሰራር ጥበባቸው ሁሉ ልዩ ነው። ሮማዎች በዛሬው አጠራር የስቶክ ገበያ የምንለው ሁሉ ነበራቸው።ሮማዊያን ግብር የሚጥሉት የሚሰሩ ሰዎችን ለመዝረፍ እና ነገዴን ለማራቆት አይደለም። በዚህም ምክንያት ሮማ የዓለም ነገዴዎች መዲና፥የሃብታቸውም መከማቻ ማዕከል ሆነች። ግዛቷም ከእንግሊዝ እስከ ቀይ ባህር ይዘልቅ ነበር።

በአምስተኛው ክ/ዘመን ሮማዊያን ሰርቶ ከመኖር የሚያላቅቅ አዲስ የገቢ ምንጭ አገኙ። ፖለቲካ!!! አዎ! ሮማዊያን ፖለቲካ የገቢ ምንጭ እንደሚሆናቸው ተረዱ። እናም ከበላይ እየነጠቀ ለተክላይ የሚሰጥ አይነት ስርዓት ለመንግስትነት መምረጥ ይህን ግኝታቸውን እንደሚያሳካላቸው አመኑ። ሮማዊያንን ያያያዛቸው የሞራል ሰንሰለት መላላት ጀመረ። የማህበረሰቡ ጠንካራ ትስስር መበጣጠስ ያዘ። ፖለቲከኞች ሳይሰሩ መብላት የሚፈልጉ ሮማዊያንን ሆድ ለመሙላት በሚሰሩ ሰዎች ላይ በግብር ስም ህጋዊ ዘረፋ ማካሄድ ጀመሩ። ከሚሰራው ይልቅ “ሳልሰራ የሚያበላኝ ካገኘሁ ምንአለፋኝ” እያለ በየቤቱ የሚቀመጠው ሰው በዛ። የሮማዊያን የሞራል ንቅዘት የገነቡትን ሪፑብሊክ መሰረቶች መሸርሸር ያዙ። ሮማዊያን ነፃነታቸውን እና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ከፍ ያደረጓትን ሮማ ወዳልሆነ አቅጣጫ መሯት። በታላቅ የነፃነት እና የሰብዓዊነት መሰረት ላይ የተገነባችው ሮም በትንሽ እና የጫጨ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ወደሚተገብሩት የአምባገነንነት ስርዓት ለመጓዝ ተገደደች። የዚያች የታላቅ ሪፑብሊክ ህዝብ ጣፋጩን የነፃነት ጣዕም መልሶ ሊያገኘው በማይችልበት ጨለማ ውስጥ ከተተው።

ኮሎሴምየሮማ መንግስት “ህዝቡን የማዝናናት ሃላፊነት አለብኝ” እስከማለት ደረሰ። እናም ያዝናናው ገባ። ህዝቡ በተገነባለት ስፍራ ሆኖ ቲያትር፥ የሰርከስ ትርኢት እንዲሁም ከሌላ ሀገር ተማርከው በሚመጡ ሰዎች መሃል በሚደረግ የጎራዴ ፍልሚያ እና ከሌላ ሀገር የሚያመጧቸውን ሰዎች በህዝብ ፊት ወሲብ እንዲፈፅሙ ማድረግ የሮማዊያን “መዝናኛ” ሆነ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በፎቶው በምታዩት የዚያ ዘመን ምርጥ የመዝናኛ ስፍራ ውስጥ ነው። የሮማ ንጉስ ይህን ህዝብን የማዝናናት ሃላፊነት ለመወጣት በአሁኑ ዋጋ ሲተመን በየዓመቱ 100ሚሊዮን ዶላር ያህል ያወጣል።

በንጉስ አንቶኒዮስ ፒዮስ ዘመን (ከ138-161 ዓ/ም) የሮማ ነጠቃ እና ዝርፊያ ጫፍ ደረሰ።ወታደሮች፥ጆሮ ጠቢዎች፥ እና የመንግስት ጋሻ ጃግሬው ሁሉ በየደረሱበት ግብር መተመንና ማስከፈል ጀመሩ። ዋናው የመንግስት ስራ ግብር እየሰበሰቡ ግብር ለማይከፍሉ ሰዎች ማደል ሆነ። በዚህም መጀመሪያ ገንዘብ ያለው ሃብታሙ፥ቀጥሎ መካከለኛ ገቢ ያለው፥ ከዚያም ድሃው ተጎዳ። ከዚህ በኋላ ሮም እንኳን ለህዝቧ ለወታደሮቿም የሚሆን ምግብ የላትም። ወታደሮች የሚበሉት ሲያጡ ግብር እየተመኑ ሲገፏቸው የነበሩትን፥ሲያሳዷቸው የቆዩትን ነጋዴዎች ባሰቡ ጊዜ አዘኑ። ምክንያቱም አሁን እንደዚያ ሊያደርጉት የሚችሉት ነጋዴ የለም።የሚሰራውን ሰው ሁሉ አራቁተዋል። በአሁኑ ዋጋ አንዱ 300ዶላር የሚያወጣ ንፁህ የብር(ሲልቨር) ገንዘብ የነበራት ታላቋ ሮማ ይሄው ገንዘቧ 95 በመቶ ጋሸበባትና የብርነት ይዘቱ ወደ 5በመቶ ዝቅ አለ። ይህ የሮማዊያንን የቁጠባ ተነሳሽነት ጨርሶ አጠፋው።ሸቀጦች ከነጋዴዎቹና ከኢንተርፕርነሮቹ ጋር ከሮም ምድር ጠፉ።ያሉት ጥቂቶችም ዋጋቸው ሰማይ ነካ። በመጨረሻም ወታደር ጦሩን ወደ ንጉሱ አዞረበት።

የሞራል፥የነፃነት እና የኢኮኖሚ መሰረቶቿን ሁሉ ንዳ የጨረሰችው ታላቋ ሮማ እኤአ 476ዓ/ም ራሷን አጠፋች። ከያኔዋ ሮማ ብዙ የምንማረው እና የምንጠነቀቀው ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ሮማዊያን መጀመሪያ ጠንካራ ሰብእናቸውን፥ከዚያ ነፃነታቸውን በመጨረሻም ስልጣኔያቸውን ሁሉ ይዘው ጠፉ።

Advertisements