ሞንት ፒለሪን፣ ሉድዊግ ኤርሃርድ፣ እና ኒዎ-ሊበራሊዝም

(By Kidus Mehalu)

⦿ ሞንት ፒለሪን – ስዊዘርላንድ 

ኦስትሪያዊው ፍሬደሪክ ሄይክ በ1938ዓ/ም በሉዊስ ሮጀር አማካይነት የተዘጋጀውን ዓይነት የምክክር መድረክ በስዊዘርላንድ አዘጋጀ። ከሚያዚያ አንድ ቀን አስራ ዘጠኝ አርባ ሰባት ዓ/ም እስከ ሚያዚያ አስር በሞንት ሚለሪን(ቫውድ) በተደረገው በዚህኛ የምክክር ስብሰባ ላይ ከአሌክሳንደር ሩስቶ በቀር በፓሪስ በተደረገው የዋልተር ሊፕማን ውይይት ታዳሚ የነበሩት ሰዎች እንዲሁም አዳዲሶቹ የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ፈርጦች ሚልተን ፍሪድማን እና ጆርጅ ስቲግለር ተገኝተዋል። የኒዎ-ሊበራሊዝም አቀንቃኞች እና የጥንቱ ሊበራሊዝም ደጋፊዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የያዙት አቋም ለምን እና እንዴት ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ማሰላሰላቸውን ቀጥለዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ውጥናቸው የከሸፈባቸው መስለው የሚታዩት ኒዎ-ሊበራሎች በእልህ እና በቁጭት እየተብሰለሰሉ ሃሳባቸውን መሰንዘር ጀመሩ። የጥንቱ ሊበራሊዝም አራማጆችም ለዓለም የሚበጃት መፍትሄ የጥንቱን ሊበራሊዝም ክፍተት በመሙላት የሚገኝ መሆኑን ለማስረዳት ሞከሩ።

ሞንትተሰብሳቢዎቹ ልዩነታቸውን ለማስታረቅ እንዲረዳቸው በአንድ ማህበር ጥላ ስር ለመስራት ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ቢያገኝም የሚቋቋመው አዲስ ማህበር ስም ግን አነታርኳቸዋል። ኒዎ-ሊበራሎቹ የማህበሩ ስም “የአዲሱ ሊበራሊዝም(ኒዎ- ሊበራሊዝም) ማህበር” እንዲባል ሲፈልጉ ሊበራሎቹ ደግሞ “የጥንቱ ሊበራሊዝም(ክላሲካል ሊበራሊዝም) ማህበር” መባል አለበት አሉ። ሁለቱም ቡድኖች በያዙት አቋም ስላልተስማሙ የማህበሩን ስም በተሰበሰቡበት አነስተኛ የስዊዘርላንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ ተራራ ስም ለመጥራት ወሰኑ። በስዊዘርላንድ የቫውድ ግዛት የሚገኘው የዚህ ተራራ ስም ‘ሞንት ፒለሪን’ ይባላል። ስለዚህ ይህንኑ ስም እንዲይዝ ተደረገና የሞንት ፒለሪን ሶሳይቲ ሚያዚያ ስምንት ቀን አስራ ዘጠኝ አርባ ሰባት ዓ/ም ተቋቋመ።

ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ የኒዎ-ሊበራሊዝም ሃሳብ አመንጭ አሌክሳንደር ሩስቶ እና የወቅቱ የምዕራብ ጀርመን ኢኮኖሚ ካውንስል ዳይሬክተር የነበረው ጓደኛው ሉድዊግ ኤርሃርድ በአባልነት ተቀላቅለውታል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጦር በተቆጣጠረው የምዕራብ ጀርመን ክፍል የኢኮኖሚ ካውንስል ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመው ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ሉድዊግ ኤርሃርድ አጋጣሚውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፅንሰ ሃሳቦችን በከፊል ተግባራዊ ለማድረግ ተጠቀመበት።

⦿ ጀርመንን ከትቢያ ያነሳት ሉድዊግ ኤርሃርድ  እና ኒዎ-ሊበራሊዝም

ሰኔ 21 ቀን 1948 ዓ/ም ሿሚዎቹን ሳያስፈቅድና ሳያማክር ናዚ ሲተገብረው የቆየውን የዋጋ ቁጥጥር፣ የሰራተኞች ዝቅተኛ ደሞዝ ጣሪያ፣ የዋጋ ቁጥጥር እና አምራቾች መንግስት የሚፈልገውን ምርት ብቻ እንዲያመርቱ ሲደረጉበት የነበረውን የምርት ቁጥጥር እንዲሁም የምግብ ዕደላ(ሬሽን) ፕሮግራም እንዲቀር መወሰኑን በሬዲዮ ያወጀው ሉድዊግ ኤርሃርድ ናዚ በጦርነቱ ምክንያት እያተመ ወደ ኢኮኖሚው ያስገባው እና የምዕራብ ጀርመን ኢኮኖሚ ሊሸከመው ከሚችለው አምስት እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ከኢኮኖሚው ውስጥ የማስወጣት ስራም ሲሰራ ቆይቷል። በዚያው ዕለት በሬዲዮ ባደረገው ንግግር ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ ይጠቀሙበት የነበረውን የድሮው ገንዘብ ‘ሪች ማርክ’ በአዲሱ ‘ደች ማርክ’ እንደሚተካና አስር ሪች ማርክ በአንድ ደች ማርክ እንዲመነዘር መወሰኑን ለህዝብ አሳወቀ።

ሉድዊግ ኤርሃርድ በብቸኝነት ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት በጀርመን የአሜሪካ ጦር አዛዥ በነበሩት ጄነራል ሉዊስ ክሌይ ፊት ተይዞ እንዲቀርብ ተደረገ። ጄነራል ክሌይም ኤርሃርድን “አማካሪዎቼ እንደነገሩኝ ከሆነ የፈፀምከው ትልቅ ስህተት ነው። ስለዚያ ምን ትላለህ?” በማለት ጠየቁት።

ኤርሃርድ በበኩሉ ለጄነራል ክሌይ “አማካሪዎችዎን አይስሟቸው። የእርሶ አማካሪዎች የነገሩዎትን ዓይነት ምክር የእኔም አማካሪዎች ነግረውኛል።” በማለት መልስ ከሰጣቸው በኋላ ወዲያውኑ ቢለቀቅም ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ በድጋሚ አሜሪካዊው ኮሎኔል ኦብረስት ፊት እንዲቀርብ ተደረገ። ኮሎኔል ኦብረስትም “ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት የዋጋ ቁጥጥር እንዲላላ ማድረግህ እና የምግብ እደላ ፕሮግራማችን እንዲስተጓጎል ማድረግህ ተገቢ ነውን? ዓላማህስ ምንድ ነው?” ብለው ጠየቁት። ludwig erhard

ሉድዊግ ኤርሃርድም “እኔ ያደረግሁት የዋጋ ቁጥጥር እንዲላላ ሳይሆን ፈፅሞ እንዲቀር ነው። የምግብ ዕደላ ፕሮግራምም ጭራሽ እንዲቀር እንጅ እንዲስተጓጎል አላደረግሁም። በጀርመን የምግብ ዕደላ ፕሮግራም የተጀመረው በዋጋ ቁጥጥር ምክንያት የምግብ አቅርቦት ችግር መከሰቱን ተከትሎ ነበር። ዓላማየ የዋጋ ቁጥጥር እንዲቀር በማድረግ ከገበያ የጠፉትን ምርቶች ወደ ገበያ እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ምግብ ለማግኘት የሚያስፈልገው ብቸኛ ቲኬት ‘ደች ማርክ’ ነው። ይህን ‘ደች ማርክ’ ለማግኘት ደግሞ የግድ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። የዚህን ውጤት ከጥቂት ጊዜ በኋላ አብረን እናይዋለን።” በማለት ለኮሎኔሉ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ጀርመን የአውሮፓ የጋራ መገበያያ የሆነውን ዩሮ ገንዘቧ ከማድረጓ በፊት ስትጠቀምበት የቆየችው ብር ‘ደች ማርክ’ ይባላል።

ይህ የኤርሃርድ ውሳኔ ቆይቶ ትክክል የነበረ እና ውጤቱም አስደናቂ ሆኖ ታይቷል። የዋጋ ቁጥጥር መነሳቱ የምርት አቅርቦት ችግርን የፈታ ሲሆን የገንዘብ ለውጡ ደግሞ የጀርመናዊያንን እህል ውሃ ሲፈታተን የነበረውን ግሽበት አቁሞታል። የዋጋ ቁጥጥር እና ተመን አለመኖር ገበያ የገዥዎችን ፍላጎት በትክክል ለሻጮች/ለነጋዴዎች እንዲደርስ ያደርጋል። የመንግስት የምግብ እድላ እና የድጎማ ፕሮግራም እንዲቀር መደረጉ ለሻጮች/ነጋዴዎች ምግብ ቢያቀርቡ ጥሩ ትርፍ እንደሚያገኙ መልክት ስለሚሰጣቸው ተፈላጊውን ምርት በበቂ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ ይነሳሳሉ።

ሉድዊግ ኤርሃርድ በተከታዮቹ ወራት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ታሪፍን ከማስወገድ ጀምሮ ከግለሰቦች የሚሰበሰብ የገቢ ግብር ከሰማኒያ አምስት በመቶ ወደ አስራ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል የተደረገ ሲሆን ከኩባንያዎች ላይ የሚሰበሰበው የገቢ ግብር ደግሞ ከስልሳ አምስት በመቶ ወደ ሃምሳ በመቶ እንዲወርድ አድርጓል። ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ከፍተኛ ወለድ በማስተዋወቅ የምዕራብ ጀርመን የገንዘብ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ እና ኢኮኖሚዋም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲመነደግ አደረገ።

አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለደቀቁ የምዕራብ አውሮፓ ሃገራት በነደፈችው የማርሻል የኢኮኖሚ ማገገሚያ እና ሌሎች እርዳታዎች ጋር ተደማምሮ ምዕራብ ጀርመን እስከ ጥቅምት ወር አስራ ዘጠኝ ሃምሳ አራት ዓ/ም ድረስ ሁለት ቢሊዮን ያህል ዶላር አግኝታለች። ሆኖም ግን ከዚህ የሚበልጥ ብዙ የማርሻል ፕሮግራም የማገገሚያ ገንዘብ ከደረሳቸው የምዕራብ አውሮፓ ሃገራት አንፃር ሲታይ የጀርመን የኢኮኖሚ እድገት ከሁሉም ፈጣን እና አስደናቂ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይህ ነው የማይባል የሞራል ውድቀት የደረሰባቸው፣ ኑሮአቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተናጋባቸው እና ተስፋ በማጣት የተጎሳቆሉት ጀርመናዊያን ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት ውስጥ ብቻ አንገታቸውን ቀና ማድረግ ችለዋል። በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ምዕራብ ጀርመን ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ቀጥሎ በዓለም ትልቁን ግዙፍ ኢኮኖሚ ገነባች።

በአስራ ዘጠኝ ስልሳ ሶስት ዓ/ም የምዕራብ ጀርመን ቻንስለር(ጠ/ሚንስትር) የሆነው ሉድዊግ ኤርሃርድ የኒዎ-ሊበራሊዝም ፅንሰ ሃሳቦችን ይበልጥ እና በስፋት ለመተግበር ዕድሉን አገኘ። የአሌክሳንደር ሩስቶ ጓደኛ እና የሉድዊግ ኤርሃርድ አማካሪ የነበረው አልፍሬድ ሙለር ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚለው ስም ከሊበራሊዝም ጋር ተቀራራቢ ስለነበር ጀርመናዊያን በጥርጣሬ እንዳያዩት እና ይህም ፍልስፍናውን ለማስፋፋት እንቅፋት እንዳይሆን በማለት ኒዎ-ሊበራሊዝምን ‘ሶሻል ማርኬት ኢኮኖሚ’[ማህበረሰብ መር ኢኮኖሚ] የሚል አዲስ ስም አወጣለት። የኒዎ-ሊበራሊዝም አቀንቃኞች ደግሞ ‘ኦርዶ ሊበራሊዝም’ እያሉ ሲግባቡበት ቆይተዋል። ኦርዶ የኒዎሊበራሎች መፅሄት ስም ነው።

የሉድዊግ ኤርሃርድ መንግስት “መንግስት በመጠኑ ጣልቃ የሚገባበት•••” የሚለውን የኒዎ-ሊበራሊዝም ፍልስፍና ክፍተት ተጠቅሞ የማህበረስብ ማሻሻያ እና የድጎማ/እርጥባን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ትልልቅ ንግድ ተቋማት እና ኩባንያዎች በቢዝነሱ ላይ የመወሰን ስልጣን ያላቸው የንግድ/የሰራተኛ ማህበራት በግዴታ እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ ሕግ አጸደቀ። የኩባንያዎች የማስፋፊያ እና የመልሶ ኢንቨስትመንት እቅድ ውሳኔ ሰጭ ባለንብረቶቹ ኩባንያዎች መሆኑ ቀርቶ መንግስት እንዲሆን የሚደነግግ አዋጅ ወጣ። ይህ የማህበረስብ ድጎማ እቅድ የመንግስት ጥገኛ የሆኑ ሰዎች እንዲበዙ በር ከፈተ። ድጎማ ከሚሹ ሰዎቹ አንፃር የመንግስት አቅም በቂ ስላልነበር መንግስት ሰራተኛው ክፍል ላይ ግብር ጨመረ። የሃገር ቤት ኩባንያዎችን ከውጭ ተፎካካሪዎቻቸው መጠበቅ በሚል ኩባንያዎቹ የኢንዱስትሪ ማህበር እንዲያቋቁሙ ተደረጎ ፍላጎታቸውን በፖለቲከኞች አማካይነት ማስጠበቅ እና የውጭ ተፎካካሪዎች በሃገሪቱ የነበራቸው ድርሻ እንዲመነምን ሆነ። ሉድዊግ ኤርሃርድ ቻንስለር ከመሆኑ በፊት ባደረገው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰው የጀርመን ኢኮኖሚ ወደኋላ መንሸራተት ጀመረ። የማህበረስብ መር ኢኮኖሚ የሚል አዲስ መጠሪያ ያገኘው ኒዎ-ሊበራሊዝም ቀስ በቀስ ጸረ ማህበረሰብ እና መንግስት እንዳሻው የሚፈነጭበት የውሸት ገበያ መር ኢኮኖሚ ስርዓት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ።

ከአስራ ዘጠኝ ሰላሳ ሁለት ዓ/ም ጀምሮ ጸረ ካፒታሊስት፣ ጸረ ሶሻሊስት እና ጸረ ኮምኒስት ሆኖ መንገድ ሲፈልግ የኖረው ኒዎ-ሊበራሊዝም ገበያ መር ኢኮኖሚን የሚያራምድ መንግስት የሚዘውረው የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስርዓት ሆኖ ብቅ አለ።ታላቁ የምጣኔ ሃብት ጠበብት ሉድዊግ ቮን ሜስስ ሂውማን አክሽን በተባለው ድንቅ መፅሃፉ ላይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ አፈር ልሶ የተነሳውን ኒዎ-ሊበራሊዝም “መሃል ቤት የቀረ፣ ፅንፈኛ ሶሻሊዝም እና የፍፁማዊ አምባገነንነት ምንጭ ነው።”ሲል ገልፆታል። ኒዎ-ሊበራሊዝም በተግባር የሕግ የበላይነት(ሩል ኦፍ ሎው) የሚከበርበት እና በንብረት ባለቤትነት መብት አስፈላጊነት የሚያምን ፣ መንግስት በፍትህ አካላት ላይ እንዳሻው የማያዝበት እና የፍርድ ትዕዛዝ የማይሰጥበት፣ የዜጎች ኢኮኖሚያዊ እጣፈንታ ለመንግስት ባላቸው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ታማኝነት የማይወሰንበት፣ በመንግስት የሚወሰን ውሳኔ እና እቅድን ሁሉም ዜጎች በተመሳሳይ ቃላት እንዲያነበንቡ የማይገደዱበት እንዲሁም ሙስናን የማያበረታታ ስርዓት ነው።

ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት በእንግሊዝ ‘ኬይኒሽያኒዝም’ እንዲወለድ ምክንያት እንደሆነው ሁሉ በጀርመንም ‘ኒዎ-ሊበራሊዝም’ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል። ሁለቱም ስርዓቶች ከሶሻሊዝም ፅንሰ ሃሳቦች ጋር ብዙም አለመራራቃቸው ደግሞ ለሶሻሊም ስርዓት መፋፋት እና ማንሰራራት ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጓል። ከአስራ ዘጠኝ ሰላሳዎቹ እስከ አስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ዓመታት ያንሰራራው ኒዎ-ሊበራሊዝም በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ እና ሰማኒያዎቹ ዓመታት ራሱን ሊገልጥ ከማይችልበት አዘቅት ወድቋል። ሆኖም ግን ዛሬ ዛሬ ይህንኑ ኒዎ-ሊበራሊዝም ትርጉሙ እንኳ በቅጡ ያልገባቸው አምባገነኖች የሚቃወሟቸውን ሊበራሎች ለማጥቃት የስድብ ምንጭ በማድረግ ከወደቀበት አንስተውታል። ዓለም ዛሬም የምትፈልገው ጡንቻቸውን ያደለቡ አምባገነኖችን ሳይሆን እንደ ኒዎ- ሊበራሊዝም አይነት አዳዲስ ሃሳቦችን እና ውጥኖችን የሚያመነጩ ግለሰቦችን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የግለሰቦች ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ከቀረ ልክ እንደ ኒዎ- ሊበራሊዝም ወድቆ ሊቀር ይችላል እንጅ በጉልበት እንደሰለጠኑት አምባገነኖች በግዴታ በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚሰለጥንበት መንገድ የለም።

Advertisements

የዓለም ኢኮኖሚ ነጻነት እና ኢትዮጵያ 

(By Kidus Mehalu)  የካናዳው ፍሬዘር ተቋም እና የዓለም የኢኮኖሚ ነጻነት ኔትወርክ በየአመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ከሰዓታት በፊት ይፋ አድርጓል።  ሪፖርቱ 159 ሃገራትን ያካተተ ሲሆን ኢትዮጵያ በዘንድሮው ሪፖርት አምና ከነበረችበት የ145ኛ ደረጃ ወደታች አንድ ደረጃ ዝቅ በማለት የ146ኛ ደረጃን አግኝታለች።  ሆንግ ኮንግ እንደ ሁሌውም የአንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሲንጋፖር፣ ኒውዚላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ አየርላንድ፣እንግሊዝ፣ ሞሪሽየስ፣ ጆርጂያ፣አውስትራሊያ እና ኢስቶኒያ ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን ተቀዳጅተዋል።  የዚህ ዓመት ሪፖርት ልዩ የሚያደርገው የመረጃው ጥንቅር በአንጻራዊነት ከሌሎቹ ዓመታት የተሟላ ሆኖ መገኘቱ እና የጾታ ዕኩልነትን ሴቶች በየሃገሩ ባላቸው የኢኮኖሚ ነጻነት አንጻር ሚዛን ላይ ተቀምጦ ለመለካት መብቃቱ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ መለኪያ ከ1 ነጥብ 0.78 ማግኘት ችላለች። የኢኮኖሚ ነጻነት እና ብልጽግና ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን በሪፖርቱ ከተካተቱ 159 ሃገራት ውስጥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚገኙ ሃገራት እና በድህነት የሚታወቁት ናቸው። የሪፖርቱን የመጨረሻውን 10ደረጃዎች የያዙት ኢራን፣ቻድ፣በርማ፣ሶሪያ፣ሊቢያ፣አርጀንቲና፣አልጀሪያ፣ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣እና ቬንዙዌላ ናቸው። ሪፖርቱ ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ዝግ የሆኑትን ሰሜን ኮሪያን እና ኩባን ከሃገራቱ በቂ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ሊያካትት አልቻለም። የዘንድሮው ሪፖርት አሜሪካ እና ካናዳን እኩል በ11ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጥ ሌሎች ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞተር ከሚያንቀሳቅሱ ሃገራት ውስጥ ደግሞ ጀርመንን በ23ኛ ደረጃ፣ጃፓንን በ39ኛ ደረጃ፣ሕንድን በ95ኛ ደረጃ፣ሩሲያን በ100ኛ ደረጃ፣ቻይናን 112ኛ እንዲሁም ብራዚልን 137ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል። ከፍተኛ የኢኮኖሚ ነጻነት ባለባቸው ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሃብታም፣የፖለቲካ እና ሲቪክ መብት ነጻነት ባለቤት እንዲሁም  የመኖር ዕድሜያቸውም ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት አንጻር ሲታይ በ25ዓመታት ያህል ልቆ መገኘቱን በጋራ ጥናት ያደረጉት የፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርስቲው ጀምስ ጉዋርቴይ፣የሳውዘርን ሜቶዲስት ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ሮበርት ላውሰን እና  የዌስት ቨርጂኒያው የምጣኔ ሃብት ጠበብት ጆሹዋ ሆል ግልጥ አድርገዋል። በሪፖርቱ ከፍተኛውን ደረጃ የተቆጣጠሩት ሃገራት ዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ 42,463የአሜሪካ ዶላር ሲሆን በሪፖርቱ ማዕከላዊ ደረጃን የተቆናጠጡት ሃገራት ደግሞ 6,036ዶላር ያህል አማካይ ገቢ ያገኛሉ። ሪፖርቱ የኢኮኖሚ ነጻነት አለባቸው ብሎ ባስቀመጣቸው ሃገራት ከሚገኙት ድሆች ውስጥ የ10በመቶ ያህሉ አማካይ ገቢ ብቻ(11,998ዶላር) የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ዜጎች ጠቅላላ የነፍስ ወከፍ ገቢ አንጻር በአማካይ ሁለት እጥፍ ይበልጣል።

ikoripoየሪፖርቱ መመዘኛዎች በሆኑት አምስት የኢኮኖሚ ነጻነት አውታሮች ውስጥ ኢትዮጵያ በሶስቱ መመዘኛዎች ያሻሻለች ሲሆን በሁለቱ ደግሞ ደረጃዋ አሽቆልቁሏል።  ሪፖርቱ ሚዛን ከ1 እስከ 10 በሚሰጥ በየተለያዩ መመዘኛዎች ነጥብ አማካይ ድምር ውጤት መሰረት የሃገራትን የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ ይዳስሳል። በሪፖርቱ የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ነጻነት መመዘኛ መነጽር ሆኖ በቀረበው የቢዝነስ ሕግጋት እና ደምቦችን እንመልከት።  ይህ መመዘኛ ለንግድ የሚውል የብድር አገልግሎት እና የወለድ ተመን ቁጥጥር፣ የስራ ቅጥር ውል እና የቅጥር ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ወለል ነጻነት መኖር አለመኖር፣ የቢዝነስ ድርጅት እና ነጋዴዎችን ገዳቢ ሕግ መኖር አለመኖር፣ ለንግድ ምዝገባ የሚወስደው ቀናት እና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ስፋት፣ የንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደት እና በዚያ ዙሪያ ያሉ ቢሮክራሲዎችን ለማለፍ የሚደረጉ ሕገወጥ የገንዘብ ክፍያዎችን ሁሉ ይዳስሳል። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ አምና ከነበራት የ6.23 ነጥብ ዘንድሮ ወደ 6.05 ዝቅ ብላለች።

ሁለተኛው መለኪያ ሚዛን ኢትዮጵያ ከውጩ ዓለም ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር የሚመለከት ሲሆን ሪፖርቱ ሃገሪቱ አምና ከነበራት የ5.22 ውጤት ወደ 5.23 ከፍ ማለቷን ያሳያል። በዚህኛው የኢኮኖሚ ነጻነት መለኪያ ሚዛን ኢትዮጵያ ወደ ሃገርቤት በሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ የምትጥለው ታሪፍ፣ የንግድ ማነቆ የሆኑ መመሪያዎች እና ደምቦች፣ በጥቁር ገበያ ላይ የሚደረግ የውጭ ገንዘቦች ግብይት ነጻነት እንዲሁም በሃገሪቱ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ነጻነት እና የውጭ ኢንቨስትመንት ገደቦች ጥልቀት ይዳስሳል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  የገበያ ተዋናዮች እና ውድድር ደካማ ከሆኑት የሃገሪቱ ተቋማት በተጨማሪ ግልጽነት እና ነጻነት የሌለበት መሆኑ ሃገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ያላትን ሕልም እስከዛሬ እውን እንዳይሆን ካደረጉት እንቅፋቶች መሃል አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ውጭ በምትልከው ቡና፣ወርቅ፣የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የቅባት እህሎች እና ሌሎች የግብርና ምርቶች አማካይነት ከዓለም ገበያ ጋር  የተቆራኘ ቢሆንም መንግስት በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት በሃገሪቱ የባንክ ሲስተም፣የካፒታል ገበያ እና የቢዝነስ ስራዎች ላይ የማያሰራ ከፍተኛ ቁጥጥር መኖር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ተጠቅማ ወደተሻለ የኢኮኖሚ እና የማህበረስብ ዕድገት ምዕራፍ እንዳትደርስ እንቅፋት ሆኗታል። የሪፖርቱ ሶስተኛው ሚዛን የገንዘብ ፍሰት መጨመር እና ግሽበትን የሚመለከት ሲሆን በዚህ ዘርፍ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት የ 5.47 ነጥብ ወደ 5.42 ነጥብ ዝቅ ማለቷን ያሳያል። አራተኛው የኢኮኖሚ ነጻነት መመዘና መህልቁን የሚጥለው በሕግ ስርዓት እና በንብረት ባለቤትነት መብት ላይ ሲሆን በዚህኛውም ሃገሪቱ አምና ካስመዘገበችው የ4.47 ውጤት ወደ 4.61 ከፍ ብላለች። ይህኛው መመዘኛው የፍትሕ ስርዓቱ እና የዳኞች ገለልተኛነት፣ የሕግ ስርዓቱ ተዓማኒነት፣የፖሊስ ታማኝነት፣ የወታደራዊ ተቋሙ በሕግ የበላይነት እና በፖለቲካው ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣የሕጋዊ ውል ጥንካሬ እና ተፈጻሚነት እንዲሁም ወንጀል በቢዝነስ ላይ ያለውን ተጽእኖ ስፋት እና ልክ በመዳሰስ በተጠቀሱት ዘርፎች ኢትዮጵያ ጥቂት ማሻሻያ እንዳረገች ይጠቁማል።

የኢኮኖሚ ነጻነቱ አምስተኛ መመዘኛ የመንግስት መጠንና ልክን ይዳስሳል። ይሄውም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ እና የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣ የመንግስት ገንዘብ አጠቃቀም እና ወጭ እንዲሁም የኩባንያ ግብር ተመንን በመቃኘት ኢትዮጵያ አምና ከነበራት የ6.11 ውጤት ዛሬ በወጣው ሪፖርት ወደ 6.62  መጠነኛ ጭማሪ አሳይታለች።በአጠቃላይ የሪፖርቱ ጥቅል መግለጫ ከአምናው አንድ ደረጃ ዝቅ ያላቸውን ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ጎራ መድቧታል። ጎረቤት ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ነጻነት ያለባት ሃገር ተብላ ስትመደብ በአጠቃላይ ጥቅል መግለጫም ኬንያ ማዕከላዊ የኢኮኖሚ ነጻነት ካለባቸው ሃገራት ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ተመድባለች። በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው ሃገር ኢትዮጵያዊያን የሚያገኙት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛው ነው። በዓለም የመጨረሻ ድሃ በሆነችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ማሽቆልቆሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂ ምሰሶ ላይ አለመቆሙን ይመሰክራል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የስትራክቸራል ችግር እንዳለበት ዓይኑን የገለጠ ሁሉ ሊያየው በሚችል ደረጃ መግዘፉም አሌ አይባልም። ይሄ የኢኮኖሚ መዛነፍም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሃገሪቱን የፖለቲካ አምድ ሲነቀንቀው ዓለም እየታዘበ ያለበት ሰውት ነው። የኢኮኖሚ ነጻነት ቁልቁል መውረድ የሕግ የበላይነት እና የፍትህ ተቋማት ነጻነት፣የሃይማኖት ነጻነት፣የሰው ሃይል ዕድገት ነጻነት፣ የሞላዊነት እና የማህበረሰብ ብልጽግና ውድቀት አመላካችም ነው። የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ነጻነት አይኖርም። ነጻነት የሌላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ደግሞ ደካማ ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ደካማ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት የሚገኙትም በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ባሉበት ሃገር ጠንካራ የመንግስት ተቋማት እና የፍትህ አካላት እንደሚኖሩ ከጎረቤት ኬንያ ማየት እንችላለን።በቅርቡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓለም ‘ትክክለኛ’ ሲል  የመሰከረለትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ‘ሕገመንግስቱን የተከተለ አይደለም!’ በማለት የምርጫ ውጤቱን ሰርዞ ሌላ ምርጫ እንዲደረግ ማዘዙ ኬንያ ያለችበትን የፍትህ እና የዳኝነት ነጻነት ከማሳየቱም በላይ ለአፍሪካ ተስፋ ፈንጥቆላት አልፏል።

***

Kidus Mehalu is the Founding Director of TEAM. TEAM is the official partner & co-publisher of the Economic Freedom Index of the World Report in Ethiopia. For more information contact us: info@teaminitiatives.org TEAM imagines a free, open, and prosperous society where individuals can live in a dignified life through entrepreneurship, responsibility, peace, toleration, and free trade.

Global economic freedom up slightly—Ethiopia ranks 146 among 159 jurisdictions 

coNEWS RELEASE-For immediate release

Addis Ababa, Ethiopia—Ethiopia ranks 146  out of 159 countries and territories included in the Economic Freedom of the World: 2017 Annual Report, released today by TEAM in conjunction with Canada’s Fraser Institute.

Last year, Ethiopia  ranked 145.

Hong Kong and Singapore again top the index, continuing their streak as 1st and 2nd respectively. New Zealand, Switzerland, Ireland, the United Kingdom, Mauritius, Georgia, Australia and Estonia round out the top 10.

“Where people are free to pursue their own opportunities and make their own choices, they lead more prosperous, happier and healthier lives,” said Fred McMahon, Dr. Michael A. Walker Research Chair in Economic Freedom with the Fraser Institute.

The 2017 report was prepared by James Gwartney, Florida State University; Robert A. Lawson, Southern Methodist University; and Joshua Hall, West Virginia University.

It’s based on data from 2015 (the most recent year of available comparable data) and measures the economic freedom (levels of personal choice, ability to enter markets, security of privately owned property, rule of law, etc.) by analysing the policies and institutions of 159 countries and territories.

This year, for the first time, the ranking is adjusted for gender equality. In countries where women are not legally accorded the same level of economic freedom as men, that country receives a lower score.

“The link between economic freedom for all citizens and the prosperity they enjoy is undeniable, while the lowest-ranked countries are usually burdened by oppressive regimes that limit freedom and opportunity,” McMahon said.

The 10 lowest-ranked countries are: Iran, Chad, Myanmar, Syria, Libya, Argentina, Algeria, the Republic of the Congo, the Central African Republic and Venezuela. Some despotic countries such as North Korea and Cuba can’t be ranked due to lack of data.

Other notable rankings include the United States and Canada, which tied at 11th, Germany (23), Japan (39), France (52), India (95), Russia (100), China (112) and Brazil (137).

According to research in top peer-reviewed academic journals, people living in countries with high levels of economic freedom enjoy greater prosperity, more political and civil liberties, and longer lives.

For example, countries in the top quartile of economic freedom had an average per-capita GDP of US$42,463 in 2015 compared to US$6,036 for bottom quartile nations.

Moreover, the average income in 2015 of the poorest 10 per cent in the most economically free countries (US$11,998) was almost twice the overall average per capita income in the least free countries. And life expectancy is 80.7 years in the top quartile of countries compared to 64.4 years in the bottom quartile.

The Fraser Institute produces the annual Economic Freedom of the World report in cooperation with the Economic Freedom Network, a group of independent research and educational institutes in nearly 100 nations and territories. It’s the world’s premier measurement of economic freedom, measuring and ranking countries in five areas: size of government, legal structure and security of property rights, access to sound money, freedom to trade internationally, and regulation of credit, labour and business.

See the full report at www.fraserinstitute.org/economic-freedom.

Ethiopia scores in key components of economic freedom (from 1 to 10 where a higher value indicates a higher level of economic freedom):

  • Size of government: changed to 6.05  from 6.23 in the last year’s report
  • Legal system and property rights: changed to5.23 from 5.22
  • Access to sound money: changed to 5.42 from 5.47
  • Freedom to trade internationally: changed to 4.61 from 4.49
  • Regulation of credit, labour and business: changed to 6.62 from 6.11

According to the 2017 EFW Index, the economic freedom score of Ethiopia declined by one levels as compared to its Rankings in 2016. A recent economic research also showed the increasing levels of foreign aid to Ethiopia negatively influence the adoption of market-oriented reforms and the overall economic freedom.

***

About the Economic Freedom Index

Economic Freedom of the World measures the degree to which the policies and institutions of countries support economic freedom. This year’s publication ranks 159 countries and territories. The report also updates data in earlier reports in instances where data has been revised. For more information on the Economic Freedom Network, datasets, and previous Economic Freedom of the World reports, visit www.fraserinstitute.org. And you can ‘Like’ the Economic Freedom Network on Facebook at www.facebook.com/EconomicFreedomNetwork.

***

TEAM is the official partner and co-publisher of the Economic Freedom Index of the World Report in Ethiopia. For more information contact us: info@teaminitiatives.org.  TEAM imagines a free, open, and prosperous society where individuals can live in a dignified life through entrepreneurship, responsibility, peace, toleration, and free trade.

ዘረኞች የፈነጠዙበት፤ዴሞክራቶች የተሸማቀቁበት የጀርመን ምርጫ! 

የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት ፓርቲ የዕሁድለቱን ምርጫ 33በመቶ በሆነ ድምጽ አሸንፏል። ይህም የሃገሪቱን ቻንስለር አንጌላ መርክልን ለአራተኛ ጊዜ ጀርመንን እንዲመሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ሆኖ የቀጠለው የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምርጫውን ቢያሸንፍም ያገኘው ውጤት ግን ከአራት ዓመታት በፊት ካገኘው 8በመቶ ያነሰ ነው። እስከዛሬ ጀርመንን ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ጋር  በጥምረት ሲመራ የቆየው የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲም 20.5 በመቶ በሆነ ውጤት የፓርላማውን ወንበር በሁለተኛነት  ደረጃ መቆጣጠር ቢችልም ይህ ግን ፓርቲው ከ1949ዓ/ም ወዲህ ያገኘው ዝቅተኛ ውጤት ነው ተብሏል። በዚህ የተበሳጩት ሶሻል ዴሞክራቶች ከእንግዲህ ጠንካራ ጥምር መሪ ሳይሆን ጠንካራ ተቃዋሚ ሆነው እንደሚቀጥሉተናግረዋል።በዚህም ምክንያት ምርጫውን ያሽነፈው የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ መንግስት ለመመስረት እና አንጌላ ሜርክልን በስልጣን ለማቆየት ከነጻ ዴሞክራቶች(10.7) እና አረንጓዴ ፓርቲ(8.9) ጋር ከመስራት ውጭ አማራጭ ያለው አይመስልም። ይህ ይሆን ዘንድ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ከራሱ ፖሊሲ ጋር የማይጣጣሙ እና የሚጋጩ የሁለቱን ፓርቲ ፖሊሲዎች ለማስታረቅ መደራደር ይኖርበታል። ከነዚህ ፖሊሲዎች ውስጥ በመንግስት ተቋማት እና በቢዝነስ ስራዎች ሁሉ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጅ የመጠቀም ግዴታ እና በቴክኖሎጂ መተካት የሚችሉ ስራዎችን  ከሰዎች የመቀማት ሃላፊነት መውሰድ፣የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የጀርመንን ኢንዱስትሪዎች ግዴታ ላይ የሚጥሉ አሰራሮችን መተግበር እና ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የመላክ ግዴታ ሳይኖርባቸው በየቤታቸው የፈለጉትን ትምህርት የማስተማር መብትን መስጠት እና እነዚህን ተማሪዎች መደበኛ ተማሪዎች የሚወስዱትን ፈተና እና ምዘና በትምህርት ተቋማት እየሄዱ በየሴሚስተሩ እንዲወስዱ ማድረግ የሚያስችል አሰራሮችን በሙሉ ወይም በከፊል የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነስ?

ይህ ካልሆነ ታላላቆቹን የክርስቲያን እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ተጋፍቶ ሳይጠበቅ የጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ቀላል የማይባል ድርሻ መያዝ ከቻለው ዘረኛው፣ጸረ እስላም ፣ጸረ ስደተኛ፣ጸረ አሜሪካ እና አክራሪ ብሄርተኛው የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ጋር ለመጋፈጥ ይገደዳሉ። የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ከተቋቋመ ገና አራት አመት ያህል ቢሆነውም አሁን ግን የጀርመንን ፓርላማ ወንበር 13 በመቶ በመቆጣጠር በሶስተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ይህ ውጤት ያስደነገጣቸው የተቀሩት የሁሉም ፓርቲ ደጋፊዎች የቀኝ አክራሪውን ዘረኛ ፓርቲ ድል እና ስር መስደድ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል። የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ሊቀመንበር አሌክሳንደር ጉላንድ ግን “ገና ምን አይታችሁ!” እያለ ነው። አሌክሳንደር እንዳለው “እኔ እና ጓደኞቼ ጀርመንን እና ህዝቧን ከወራሪ ስደተኞች መልሰን እስክንነጥቅ ድረስ እንቅልፍ የለንም።አንጌላ ሜርክልንም ማጥቃታችንን አናቆምም።” ብሏል። ከዚህ በፊት በጀርመን ፖለቲካ እና ምርጫ ውስጥ ተሳትፈው የማያውቁ ከ1.5 ሚሊዮን ዘረኛ ደጋፊዎችን በማቀናጀት ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የተሳተፈው የዘረኞች ፓርቲ ከሌሎቹ ሁሉ የተሻለ ድምጽ ማግኘት ችሏል። የቀኝ አክራሪ ብሄርተኛው፣ዘረኛው እና ጸረ ስደተኛው የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ያገኘው ውጤት አንጌላ ሜርክልንም ሳያስደነግጣት አልቀረም። እናም ጀርመንን ለ12 ዓመታት የመራችው ቻንስለር አንጌላ መርክል ከምርጫው “የኤኤፍዲን(የአማራጭ ፓርቲውን) ደጋፊዎች ስጋታቸውን በማስዎገድ እና ፍርሃታቸውንም በመጋራት ከጥላቻ በራቀ ፖለቲካ ወደ እኛ እናመጣቸዋለን።”ስትል ደስታ ከራቀው ፊቷ ጋር በቴሌቪን መስኮት ታይታለች። የዘረኛው ፓርቲ ሊቀመንበር እና አርክቴክት ለንግግሯ ምላሽ እንዲህ አለ። “ለአንጌላ ሜርክል እና ጀርመንን ለጀርመናዊያን ብቻ እንዳትሆን ለሚሰሩ እንዲሁም በስደተኞች ለሚያስወርሩን ፓርቲዎች ሁሉ የጭቃ ላይ እሾህ ሆነን እንቀጥላለን።አናስተኛቸውም።” የሆነ ሆኖ በለየለት የምስራቅ ጀርመን አምባገነን ሥርዓት  ውስጥ ተወልዳ ያደገችውን አንጌላ መርክል የፖለቲካ ሕይወት ጅማሮ እጇን ይዞ እየመራ ያስገባት የቀድሞው ቻንስለር ሄልሙት ኮህል ዛሬ ለደረሰችበት ስኬቷ ትልቅ ሚና መጫወቱ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። “የኔ ውድ!” እያለ የሚያቀናጣትን ይህችን ሴት አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ደርሳ ማየቱ ጀርመንን ለ16 ዓመት ያህል የመራትን ቻንስለር ሄልሙት ኮህል እጅግ ያስደስተው እንደነበር በቅርቡ ሕልፈቱን ተከትሎ የወጣው የህይወት ታሪኩን የሚዳስስ መጽሃፍ ላይ ሰፍሯል። ሌላው ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት የወጣው የጀርመን ቻንስለር ደግሞ ኮንራድ አዴናውር ሲሆን ሃገሪቱን ለ14 ዓመታት ያህል አገልግሏል። አንጌላ መርክልም እንቅፋት ሳይገጥማት ማለትም ፓርቲዋ ከግሪን እና ነጻ ዴሞክራቶች ጋር ተስማምቶ መጣመር ከቻለ ጀርመንን ለ16 ዓመታት ያህል በቻንስለርነት/በጠቅላይ ሚንስትርነት የማገልገል ዕድሉ ይፈጠርላታል። ይህ ብቻም አይደል። እንደ ዶናልድ ትራምፕ፣ኤርዶጋን፣ ፑቲን እና ኪም ለመንገስ በሚሯሯጡበት ዓለም ውስጥ ለዓለም ሰላም ጠበቃ በመሆን የነጻው ዓለም ትልቅ ድምጽ የመሆን ሃላፊነት ተጥሎባታል።ይህን ሃላፊነት ሊጋራት የሚችል ሌላ አንድ ሰው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን ነው።  በአጠቃላይ ሲታይ ግን የትናንቱ(የእሁዱ) የጀርመን ምርጫ ዘረኞችን ያስፈነጠዘ ፤ዴሞክራቶችን ደግሞ ያሸማቀቀ ነበር ማለት ይቻላል።

አንስታይን፣አሜሪካ እና ጃፓን:-የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ!

(By Kidus Mehalu) እኤአ ከ1894ዓ/ም እስከ 1895ዓ/ም በጃፓን እና በቻይና በተደረገው ጦርነት በአውሮፓዊያን ይሰለጥን የነበረው የቻይና ሰራዊት ክፉኛ ተመቶ ጃፓን በቢጫ ባህር እና በኮሪያ ላይ ከመንገሷም ታይዋንን ተቆጣጠረች። ይህም አልበቃ ብሏት በቻይና እና ራሽያ መሃል የሚገኘውን ስትራቴጅክ ቦታን በእጇ አደረገች። ይህ ቦታ ማንቹሪያ ይባላል። ሩሲያ “ማንቹሪያ የቻይና ነው” በማለት በ1904 ከጃፓን ጋር ጦርነት ውስጥ ገባች። በራሽያ ድንገተኛ ጥቃት ማንቹሪያን የለቀቀችው ጃፓን በባህር ኋይሏ አማካይነት በአጭር ጊዜ የራሽያ ወታደሮች ዋና መተላለፊያ የባቡር መስመር እና የአርተር ወደብን በመቆጣጠር ለውጊያ ወደ ስፍራው ያቀኑ የነበሩትን የራሽያ የጦር መርከቦች በሙሉ ሳያስቡት አወደመችባቸው። ራሽያ ለቻይና አግዛ ገብታ የራሷ ግዛት የነበረውን የአርተር ወደብን በይፋ የጃፓን ነው ብላ ከማወጅ በተጨማሪ ኮሪያም የጃፓን መሆኑን ዕውቅና እንድትሰጥ ተገደደች። ከአምስት ዓመታት በኋላ እኤአ በ1910ዓ/ም ጃፓን ከቻይና ጋር ባደረገችው ጦርነት ያወጣችውን ወጭ እንድትከፍል ከማስገደዷም በላይ የቻይና ግዛት የነበረችውን ኮሪያን በራሷ አንደበት “ኮሪያ የጃፓን ግዛት ናት!” አስባለቻት። ይህ ሽንፈት እና ውርደት ያንገበገባት ቻይና ከ21ዓመት በኋላ ጃፓንን ለመበቀል ጦርነት ከፈተች። በዚህኛው ጦርነት 20ሚሊዮን ቻይናዊያን ካለቁ በኋላ ጃፓን የቻይናን ዋና ከተማ ተቆጣጥራ የራሷን አሻንጉሊት መንግስት አቋቋመች። ቻይናዊያን በገዛ አገራቸው ጎዳናወች እና መተላለፊያዎች ላይ“ቻይና እና ውሻ በዚህ ማለፍ አይችልም” በሚሉ የጃፓናዊያንን ጽሁፎች አንገታቸውን ደፉ። የቻይና ሴቶችም በሕግ የጃፓን ወታደሮች መጫወቻ እንዲሆኑ ተደረገ።ታዲያ ቻይናዊያንን ከጃፓን ማን ነጻ አወጣቸው?

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ራሽያ ከጀርመን፤ቻይናም ከጃፓን ነጻ የወጡበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። ታህሳስ 7 ቀን 1941 ዓ/ም ጃፓን በሃዋይ ግዛት ‘ፐርል ሃርበር’ የሚገኘውን ትልቁን የአሜሪካ ባህር ሃይል እና የሂካም አየር ሃይል ጣቢያ ማውደሟን ተከትሎ አሜሪካ በጀርመን፣በጃፓን እና በጣሊያን ላይ ጦርነት አወጀች። አሜሪካ በሌላ ሃገር ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ የሚከለክላትን የ “ኒውትራሊቲ አክት” እንዲሻር ተደርጎ በሶስቱ ሃገራት የተጠቁ እና የተወረሩ ሃገራት ራሳቸውን ነጻ ማውጣት ይችሉ ዘንድ የጦር ተሽከርካሪዎች፣የተዋጊ አውሮፕላኖች እና ካሚዮኖች እንዲሁም ስንቅና የጦር መሳሪያ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተወሰነ። ስታሊን ጀርመንን ለማሸነፍ ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ጋር መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን በመቀበል የአሜሪካ ‘ሌንድ ሊዝ’ ስምምነት ተጠቃሚ ሆኗል። በስፋት በዓለም ትልቋ ሃገር የሆነችውን ሩሲያ ከጀርመን ወረራ ለመታደግ ከ1941ዓ/ም ጀምሮ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስካበቃበት 1945ዓ/ም ድረስ ሶቬት ህብረት 11.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ አገኘች።ከዚህ በተጨማሪ  ሶቬት ህብረት 427 ሽህ 284 ስንቅ የሚያቀርቡ ካሚዮኖች፣ ከ11ሽህ በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ 35ሽህ 170 ሞተር ሳይክሎች፣ ከ4ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ስኳር፣ ስጋ፣ ጨው እና ዱቄትን ጨምሮ 120 ታንኮች እና 18ሽህ700 የጦር አውሮፕላኖች በእርዳታ አግኝታለች።በዚሁ ስምምነት መሰረት እንግሊዝ 31.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ፈረንሳይ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ሲያገኙ ቻይና ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ከአሜሪካ ማግኘት ችለዋል። አግኝተዋል። ከእርዳታው በቀር ሩሲያ ከጀርመን ጋር እንዲሁም ቻይና ከጃፓን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት ግን በአብዛኛው ለራሳቸው የተተወ ነበር።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውድማን በሰሜን አፍሪካ፣ምዕራብ አውሮፓ እና አውስትራሊያን ከጃፓን ወረራ ለመታደግ በተደረገው ትንቅንቅ ውስጥ አሃዱ ብላ የተቀላቀለችው አሜሪካ ጀርመን እንጅ ጃፓን ያን ያህል ታስቸግራለች ብላ የገመተች አትመስልም። ይህንኑ የጀርመን ፍራቻ በተለይም አልበርት አይንስታይን “ናዚ የአቶም ቦምብ ሊሰራ ይችላል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አሜሪካንም ቢሆን ከናዚ የሚታደጋት አታገኝም።” በማለት ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልትን በማሳመናቸው የማንሃተን ፕሮጀክት እንዲጀመር ተደረገ። ከሁለት ዓመት በኋላ የፕሮጀክቱን ሂደት እና ስኬታማነት እርግጠኛ እየሆኑ ሲመጡ አልበርት አይንስታይን እና ሊዮ ዚላርድ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት “አቶሚክ ቦምቡ የአሜሪካን ጠላቶች በጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ እጅ እንዲሰጡ ማድረጊያ ለማስፈራሪያ ብቻ የሚውል ነው።” በማለት ዕቅዳቸውን ተናገሩ። ይሄውም የሚደረገው ሰው በማይኖርበት ቦታ ላይ በመጣል “እንደዚህ ከምናረጋችሁ እጅ ስጡ!” በማለት ሊሆን እንደሚችል ዝርዝር ሃሳብ አቀረቡ። ይህን ዝርዝር ሃሳብ በቅጡ ማንበብ እንኳ ሳይችሉ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ሞት ቀደማቸው። ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን ስልጣኑን ተረከቡ።

ጃፓን ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በኤዥያ ተረጋግተው ተቀምጠው ለነበሩ አውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች ራስ ምታት መሆኗን ቀጥላለች። በአውሮፓ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን ሽንፈት ሲቋጭ ከማንሃተን ፕሮጀት ተሳታፊ ሳይንቲስቶች ውስጥ ኤድዋርድ ቴለር የአቶም ቦምብ መስራት የሚያስችለውን ቀመር ከአንስታይን E=MCውስጥ ለይቶ ማግኘት ቻለ። በዚሁም መሰረት የተቀመረው የአቶም ቦምብም በኒው ሜክሲኮ ስኬታማ ሙከራውን አደረገ። የጀርመንን ሽንፈት ተከትሎ ከራሽያ፣ከቻይና፣ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ መሪዎች ጋር በበርሊን የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስለ አቶም ቦምቡ ስኬታማ ሙከራ በስልክ ተነገራቸው። በዜናው በጣም የተደሰቱት ሃሪ ትሩማን አብረዋቸው ለነበሩት መሪዎች “ጃፓንን ከዚህ በፊት እናንተም ሆነ ዓለም ዓይቶት በማያውቀው መሳሪያ ልንቀጣት ነው?ምን ትላላችሁ?” ሁሉም በአንድ ድምጽ በተለይም በተለያየ ጊዜ በጃፓን ሽንፈት እና ውርደትን የተከናነቡት ቻይና እና ሩሲያ “ዛሬውኑ አድርጉት!ትመታ” ሲሉ ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጡ።

“የአቶም ቦምቡ ሰዎች በማይኖርበት ቦታ በመጣል ጃፓንን እጅ እንድትሰጥ መጠየቅ ይሻላል” የሚለውን የአልበርት አይንስታይን እና የጓደኞቹን ሃሳብ ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን አልተቀበሉትም። ፕሬዝዳንቱ እና የጦር አዛዦቹ የአሜሪካን ሃያልነት ለዓለም ለማሳየት እና ጠላቶቿን ለማሸማቀቅ የተሻለ አማራጭ ባሉት እና  ቦምቡን በቀጥታ ጃፓናዊያን ላይ መጣል በሚለው ሃሳብ ተስማሙ። እኤአ ነሃሴ 6 ቀን 1945 ዓ/ም በጃፓን ሄሮሽማ ውስጥ የመጀመሪያውን የአቶሚክ ቦምብ ጣለች። ጃፓኖች ብቻ ሳይሆኑ የተቀረው ዓለም ሁሉ ደነገጠ። በአንድ ጊዜ ከመቶ ሽህ በላይ ሰዎች አለቁ። ጃፓናዊያን “የተኛውን ትልቅ አውሬ የቀሰቀስነው በገዛ እጃችን ነው።” አሉ። ጃፓን በይፋ በጦርነቱ መሸነፏን አምና እጅ እንድትሰጥ አሜሪካ ጠየቀች። ጃፓን ግን አሻፈረኝ አለች። እኤአ ነሃሴ 9 ቀን 1945 ዓ/ም ማለትም የመጀመሪያው አቶሚክ ቦምብ ከተጣለ ከሶስት ቀናት በኋላ ናጋሳኪ ተደገመች። ይህኛው የአቶም ቦምብ የመቶ ሽህ ህዝብ ህይዎት ቀጠፈ። ከስድስት ቀናት በኋላ ኦገስት 15 ቀን ጃፓን እጅ እንደምትሰጥ በማስታወቅ ልክ የዛሬ 72ዓመት በዛሬው ቀን ማለትም ሴፕቴምቤር 2 ቀን 1945ዓ/ም ይህንኑ ሽንፈቷን በኦፊሴል በፊርማዋ አረጋገጠች።ይህን ተከትሎ ቻይና፣ኮሪያ እና ራሽያን ጨምሮ የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ ሃገራት በሙሉ በጃፓን የተነጠቁትን ሉዓላዊ ግዛታቸውን መልሰው ማግኘት ቻሉ።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲገባደድ አሜሪካ ለሩሲያ ከሰጠችው የገንዘብ ብድር ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ዶላሩን እንድትከፍል ጠይቃታለች። ሆኖም በግንቦት 1942ዓ/ም በመርከብ ለክፍያ ወደ አሜሪካ የላከችው 45ሽህ ኪሎ ግራም ወርቅ፣ ጦርነቱ እስኪገባደድ ድረስ በበርካታ መርከቦች እየተጫነ ወደ አሜሪካ የሄደው የሩሲያ ውድ ማዕድን እና ጥሬ ሃብት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሩሲያ 722ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጥራጥሬ በተለያየ ጊዜ ወደ አሜሪካ ለመላክ ተስማምታ የተቀረው ዕዳዋ እንዲሰረዝላት አድርጋለች። ከጦርነቱ የተረፉት የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች በሙሉ ሶቬት ህብረትን ጨምሮ ለ44 ሃገራት እንዲከፋፈል ተደርጓል። ብዙም ሳይቆይ ግን አሜሪካ እና ሶቬት ሕብረት እርስ በርስ እንደ ጠላት መተያየት ጀመሩ።

የሆኖ ሆኖ አሜሪካንን ከፕሮፖጋንዳ ባለፈ ፊትለፊት ጦርነት ገጥማ አቅሟን የተፈታተነች የምድራችን ብቸኛ ሃገር ጃፓን ናት። በዚህም ምክንያት የኑክሌር ጦር መሳሪያ አረር የነደደባት ብቸኛ ሃገርም መሆን ችላለች።  የጃፓንን እና የጃፓናዊያንን ያህል የኑክሌር ጦር መሳሪያን አደገኛነት በተግባር የሚያውቅ የለም። ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ውድድር ወቅት አድናቂዎቹ እና ደጋፊዎቹ “የሃሪ ትሩማንን ወኔ የታጠቀ ጀግና”  እያሉ ሲያቀማጥሉት ነበር። የሃሪ ትሩማን ወኔ የአቶም ቦምብን በንጹሃን ላይ የማዝነብ ድፍረት ነው። ትራምፕ ይህ ድፍረት ካለው በማን ላይ እና በምን ምክንያት ሊጠቀመው እንደሚችል ለጊዜው ከብዥታ የጠራ መልስ የለም። ለማጠቃለል ያህል ከቀናት በፊት በአንድ ታዋቂ የጀርመን ሚዲያ ላይ ቃለመጠይቅ ያደረገችው የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ስለ ትራምፕ እና አሜሪካ ይሄን ብላለች። “ከ12 የራሱ ፓርቲ ዕጩዎች ውስጥ   በብቸኝነት በመውጣት እና ድፍን ዓለም የተቃውሞ ድምጽ እያሰማበት የምርጫ ውድድሩን በአሸናፊነት የተወጣ ሰው ማክበር ግዴታየ ነው። ከትራምፕ ጋር የሃሳብ ልዩነት ቢኖረኝም ከሱ ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት እንደ አንጌላ መርክል ሳይሆን እንደ ጀርመን ጠቅላይ ሚንስትር ነው። ስለዚህ የጀርመንን ፍላጎት ለማስጠበቅ እሰራለሁ። ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረግ ጦርነት በዓለም ትልቅ የሆነውን የንግድ መስመር ስለሚያውክ ከማንም አውሮፓዊ አገር በላይ ጀርመንን ይጎዳል።ስለዚህ አሜሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ከማጠናከር ውጭ አማራጭ የለንም።በአሁኑ ወቅት ለእኔ አሜሪካ ከቆሰለ አውሬ ጋር ትመሳሰልብኛለች።ሁሉም ነገር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው።ጀርመን ግን ሁሉም ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ትጥራለች።”

 

ወተት  የሚጡት ዝሆኖች — የንብረት ባለቤትነት መብት እና የአካባቢ ጥበቃ!

(By Kidus Mehalu)

የንብረት ባለቤትነት መብት መረጋገጥ ለአካባቢ እንክብካቤ እና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ እና የማይተካ ሚና ይጫወታል። እንዴት የሚለውን በዝርዝር እንመልከት። እስከ አስራ ዘጠኝ ዘጠና ዓ/ም ናሚቢያ የምትገዛው ደቡብ አፍሪካን ጠፍንጎ በያዘው በዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት ነበር። የናሚቢያ ዜጎች የኔ የሚሉት ነገር አልነበራቸውም። ህይዎታቸው፣ ንብረታቸው፣የዱር አራዊቱ ሁሉ የአፓርታይድ አርክቴክቶች (የዘረኞቹ ነጮች) ነበሩ። የናሚቢያ ዜጋ በልቶ ከመተኛት ውጭ ምንም የተፈቀደለት ነገር አልነበረም። የሚዘሩት እህል በዝንጀሮ ሲበላ፣ ሰብሎቻቸው የዱር አራዊት መፈንጠዣ ሲሆን እና የቤት እንስሳቶቻቸው በአውሬ ሲበሉባቸው መከላከል አይችሉም ነበር። ምክንያቱም ዘረኛው ስርዓት (አፓርታይድ) ከሰዎቹ የበለጠ ለዱር አራዊቱ መብት በመስጠቱ ነው። የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰና እኤአ በአስራ ዘጠኝ ዘጠና ዓ/ም ናሚቢያዊያን ከዘረኛው ስርዓት ነጻ መውጣት ቻሉ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የናሚቢያ ዜጎች ሰብሎቻቸው በአራዊት እንዳይጠፋባቸው መከላከል ጀመሩ። ናሚቢያዊያን አራዊቱን እያሳደዱ መግደል ተያያዙት። የዱር አራዊቱ ቁጥር ክፉኛ ተመናመነ። ይህም የናሚቢያን መንግስት ይበልጥ ስላሳሰበው እኤአ በአስራ ዘጠኝ ዘጠና ሰባት ዓ/ም የዱር አራዊቱን ማስተዳደርን የሚመለከት አዲስ አሰራር ይፋ አደረገ። አዲሱ አሰራር የዱር አራዊት በሚበዙበት አካባቢዎች የሚገኙ ሃምሳ ማህበረሰቦች የዱር አራዊቱን በመንከባከብ እና በመጠበቅ የሚገኘውን ገቢ ለራሳቸው እንዲዎስዱ ይፈቅዳል። በውጤቱም የሚደንቅ ለውጥ መጣ። የናሚቢያ ሰው የዱር አራዊቱን በመግደል ፋንታ እንደ ፍየል እና ላም ይጠብቅ ገባ። ይሄም አልበቃቸው። የዱር አራዊቱ ወደ ሌላ ስፍራ እንዳይሄዱባቸው አካባቢውን በአጥር አጠሩ። ናሚቢያዊያን ለሌሎች ማህበረሰቦች የዱር እንስሳቱን በመሸጥ እና ከጎብኝዎች ላይ ገቢ ማግኘት ጀመሩ። ለወጣቶቻቸው ስራ መፍጠር ቻሉ።

ናሚቢያዊያን ቀደም ሲል የዱር አራዊቱን ሲገድሏቸው የነበረው የህዝብ ንብረት እና የአገር ሃብት መሆናቸው ጠፍቷው ሳይሆን ናሚቢያዊያኑ የኔ የሚሏቸው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ያፈሰሱባቸውን የእርሻ ሰብል እና የቤት እንስሳት መሆኑ ነው። ምክንያቱም በዱር አራዊቱ ላይ የባለቤትነት መብት ስለሌላቸው ግዴለሾች ናቸው። የእኔ የማይሏቸው እንስሳት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ያፈሰሱባቸውን የእኔ የሚሉት ንብረታቸውን ሲያጠፉት ዝም ብለው ማየት አይሹም። ስለዚህም ንብረቶቻቸውን ከዱር አራዊት ይከላከላሉ። እስከመቼ? የዱር አራዊቱ የእነሱ ንብረት መሆናቸውን በህግ እስኪያረጋግጡ ድረስ ማለት ነው። የዱር አራዊቱን በባለቤትነት መያዛቸው በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ይረጋገጣል።

አንደኛ ❒ በዱር አራዊቱ በብቸኝነት መጠቀም ሲችሉ፣
ሁለተኛ ❒ የዱር አራዊቱን ከወንበዴ እና ከነጣቂ የሚጠብቅ ጠንካራ ህግ መኖሩ፣እና
ሶስተኛ ❒ የዱር አራዊቱን ለሌላ ማስተላለፍ፣ መሸጥ ወይም መለወጥ ሲችሉ ነው።

ናሚቢያዊያን ሶስቱንም ማድረግ ችለዋል። ከዚህ በተረፈ ከፓርክ የሚገኝ ገቢን ወደ ማህበረስቡ የሚደርስበት መንገድ ከሌለ አንድን የዱር እንስሳት ፓርክ ‘የህዝብ ንብረት ነው።’ በማለት ብቻ የቱሪዝም ገቢውን ማሳደግም ሆነ ከፓርኩ ተገቢውን ያህል ሃብት ማመንጨት አይቻልም። ይሄን ለመረዳት ስንቅዎን ይዘው በመንግስት በሚተዳደሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ፓርኮች ይሂዱና ጉብኝት ያድርጉ። ከዚያም ላም፣ ፍየል፣ በሬ፣ ግመል፣ በርካታ የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት፣ ማህበረሰቦቹ በፓርኩ ውስጥ የገነቧቸውን ጎጆዎች እና በእነዚህ የማህበረሰብ አባላት የተገደሉ ብዙ የዱር እንስሳትን ይመለከታሉ። ይህም ብቻ አይደለም፤ራሱ መንግስት አንዳንዶቹ ፓርኮች “የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል” ሲል እየሰማን ነው። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያዊያኑ የአካባቢው ሰዎች እንደ ናሚቢያዊያኑ ሁሉ የዱር አራዊቱ የህዝብ እና የሃገር ንብረት መሆናቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። የዱር እንስሳት መግደልም በህግ የተደነገገ ወንጀል መሆኑንን ብዙዎቹ ይረዳሉ። ሆኖም ግን የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለራሱ እና ለኔ ለሚለው ነገር ቅድሚያ ይሰጣል። ስለዚህም ይህን ተፈጥሮአዊ ባህሪውን በሕግ እና በአዋጅ ማፋለስ ስለማይቻል ተፈጥሮአዊ የሆነው የንብረት ባለቤትነት መብቱ በጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ድጋፍ ሊሰጠው እና ሊከበርለት ይገባል።

በአጠቃላይ ከናሚቢያ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመንግስት ከሚተዳደሩ ብሄራዊ ፓርኮች ይልቅ በግል የሚተዳደሩ የእንስሳት ጥበቃ መጠለያዎች እና ፓርኮች ሁሌም የተሻሉ ናቸው። በደቡብ አፍሪካም ስኬታማ እና ውጤታማ የሚባሉት ፓርኮች በሙሉ የግል መሆናቸው ይታወቃል። ለምሳሌ በፎቶው ላይ ወተት ሲጠጡ የምትመለከቷቸው ዝሆኖች በኬንያ መንግስት ከሚተዳደሩት ፓርኮች ውስጥ የዝሆን ጥርስ በሚያድኑ ሰዎች በመገደላቸው እና ተገቢውን ጥበቃ ባለማግኘታቸው ምክንያት ናይሮቢ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የግል መለስተኛ የዝሆኖች መጠለያ እና ፓርክ ውስጥ የተዛወሩ ናቸው።ይህን  ልምድ“10ቢሊዮን ብር ለወጣቶች ስራ ፈጠራ መድቢያለሁ” ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ከተጠቀመበት በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን መምታት የሚችልበት ዕድል ይመስለኛል። አንደኛ እኩል ተነሳሽነት፣ብቃት፣ችሎታ እና ዝግጅት የሌላቸውን ወጣቶች በማደራጀት ብዙ ገንዘብ በመስጠት አስተማማኝ እና ዘላቂ ያልሆነ ኢንቨስትመንት ላይ የህዝብ ገንዘብ እንዳያባክን ይረዳል። ሁለተኛ መንግስት ራሱ ለአደጋ ተጋልጠዋል ያላቸውን ፓርኮች መታደግ ከማስቻሉ በተጨማሪ በእነዚህ ፓርኮች ላይ መንግስት የሚያወጣውን ወጭም ማስቀረት ይቻላል። ሶስተኛ ደግሞ ለወጣቶቹ አስተማማኝ ስራ እና ዘላቂ ገቢ ከማስገኘት አልፎ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለሃገር ማመንጨት እንደሚቻል መገመት አያዳግትም። እርሶ ይህን ሃሳብ እንዴት ያዩታል?

ወዶአ.jpg

(©Kidus Mehalu) እኤአ ነሃሴ 15 ቀን 1971 ዓ/ም ከገንዘብ ሚንስትራቸው ጆን ኮናሊ፣ የብሄራዊ ባንኩ ሊቀመንበር አርተር በርንስ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው ሄርበርት ስቴይን እና ፖል ቮከር ጋር ሆነው በጉዳዩ ላይ በካምፕ ዴቪድ ሲመክሩ የዋሉት ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ምሽቱን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ዓለም ለአጭር ደቂቃ ጆሮ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ንግግራቸውን ቀጠሉ። እንዲህም አሉ። “የአሜሪካን ዶላር ያከማቻችሁ ሃገራት ሆይ ከንግዲህ ዶላርን በወርቅ ለውጡን ብላችሁ ወደኛ እንዳትመጡ። ከዛሬ ጀምሮ የብሪቶን ውድስ ስምምነት አይሰራም። ስለዚህም ዶላርን በወርቅ አንቀይርም።ንግግሬን ጨርሻለሁ፤ አመሰግናለሁ።” በማለት ከቴሌቪዥኑ መስኮት ተሰወሩ።

ዶላር ሲያከማቹ የነበሩ ሃገራት ሁሉ ግን የሰሙትን ለማመን ተቸግረው ከቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ ዞር ለማለት ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። አውሮፓዊያኑ በዶላር ላይ ፊታቸውን በማዞር በፍጥነት የራሳቸውን ገንዘብ በአነስተኛ የምንዛሬ መወዛወዣ (ፍሎቲንግ ሬት) ክፍተት ዋጋውን እየተመኑ ለመስራት “ዩሮፒያን ስኔክ” የሚባል ፕሮጀክት ጀመሩ። የአውሮፓዊያኑን ፕሮጀክት ለማምከን አሜሪካ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዶላርን ዋጋ ዝቅ (ዲቫሉየት) በማድረግ እና ዓለም ከአውሮፓዊያኑ ገንዘብ የበለጠ ዶላርን እንዲጠቀሙ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መወዛወዣ ክፍተቱንም አሰፋችው። ይህ የአሜሪካ ስትራቴጅ “የአውሮፓዊያኑ እባብ” ብዙ ርቀት እንዳይሄድ ያደረገ ዘንዶ ነበር። አውሮፓዊያኑ አንድ ዓመት ያህል እንደተጓዙ እንግሊዝ መሃል መንገድ ላይ ዘንዶው ማድፈጡን ተመለከተችና ቶሎ እራሷን አገለለች። ጣሊያን ተከተለቻት። የአውሮፓዊያኑ ስኔክ ፕሮጀክት ፈረሰ። የዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ግሽበት፣ የስራ አጥ ቁጥር እና የዋጋ ንረት በድጋሚ ተናጋ።

በታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደቀቀችው አውሮፓ ግን ሌላ የኢኮኖሚ ቀውስ መቋቋም የሚያስችል አቅም አልነበራትም። ስለዚህም በወርቅ ይቀየርልናል ብለው እንደ ገንዘብ ሲገበያዩበት እና ሲያከማቹት የነበረውን የአሜሪካ ዶላር አለመቀበል ማለት ሲገነቡት የኖረውን ኢኮኖሚ በመናድ ለዳግም የኢኮኖሚ ውድቀት መዳረግ መሆኑን ተረዱ። ለወትሮውም በዓለም ንግድ እና ኢኮኖሚ ላይ እዚህ ግባ የማይባል ድርሻ የነበረው የተቀረው የዓለም ክፍልም ፊቱን ወደ ዶላር ከመመለስ በቀር ምንም ምርጫ እንደሌለው ተረዳ። አሜሪካ አንድም ወታደር ሳትጠቀም ዓለምን እንዲህ አስራ ያዘች። ይህም ብቻ አይደለም።

ዶላር ዓለማቀፍ ገንዘብ መሆኑ አሜሪካ የትም ሃገር አንዲት ሳንቲም ሳታወጣ የፈለገችውን መግዛት አስችሏታል። በቃ! እዳ እንዳለባት የሚገልፅ ህጋዊ ወረቀት ትሰጣለች። ሃገራት ያን ወረቀት እንደ ገንዘብ ያዘዋውሩታል። ምክንያቱም የአሜሪካ ዶላር ሁሉም የሚቀበለው ዓለም ዓቀፍ ገንዘብ ነው። በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር እዳ ያለባት ሃገር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ስትሰጥ የምናያትም በዚሁ ምክንያት ነው።ይህንኑ ዶላር ያስቀየማትን ለመቅጫም ትጠቀምበታለች። ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ገንዘብ ባተመች ቁጥር ሁሉም የዓለም ሃገራት የግሽበቱን ፅዋ አብረው ለመቋደስ ይገደዳሉ። ሌላስ? ሌላው ደግሞ ዶላር ዓለም አቀፍ ገንዘብ እና የዋጋ ማንጸሪያ መሆኑ በዓለም ላይ አሜሪካን የውጭ ምንዛሬ ክምችት የማያስፈልጋት ብቸኛ ሃገር አድርጓታል።ይሁን እንጅ በወርቅ ክምችትም ቢሆን አሜሪካ ያላትን ግማሽ ያህል እንኳ ያለው ሌላ ሃገር የለም። ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጀርመን 3374 ቶን ወርቅ ክምችት ያላት ሲሆን ይኸውም የሃገሪቱን 70በመቶ ያህል የውጭ ምንዛሬ ክምችት ይሸፍናል። ጣሊያን፣ፈረንሳይ እና ቻይናም በብሄራዊ ባንኮቻቸው አማካይነት በተከታታይ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያለውን የዓለምን የወርቅ ክምችት ይዘዋል። አብዛኛው የእነዚህ ሃገራት የወርቅ ክምችት የሚገኘውም በኒውዮርክ/ፌደራል ሪዘርቭ/ ውስጥ ከፊሉ ደግሞ የዓለም የገንዘብ እና የወርቅ ግብይት በሚካሄድባቸው እንደ ለንደን እና ፓሪስ ወዘተ ባሉ ስፍራዎች ነው። ለምሳሌ የጀርመን 37በመቶ የወርቅ ክምችት በኒውዮርክ ሲገኝ 13 በመቶ ደግሞ በለንደን ይገኛል። ሃገራቱ ይህን  የሚያደርጉት የውጭ ምንዛሬ ችግር ሲገጥማቸው የወርቅ ክምችታቸውን በፍጥነት ወደ ዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ በማቅረብ እንዲሸጡ እና የውጭ ምንዛሬ(ዶላር) እንዲያገኙ ስለሚረዳቸው ነው። ለማብራራት ያህል 3374 ቶን የወርቅ ክምችት ያላት ጀርመን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢገጥማት እና ይህን የወርቅ ክምችቷን አሁን ወርቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ባለው ዋጋ ብትሸጠው ለሃገሪቱ በቀጥታ 132 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር(ሃርድ ከረንሲ) ያስገኝላታል ማለት ነው።

አሜሪካ ዶላርን በወርቅ እየቀየረች ዓለምን አጓጉታ በወጥመዷ ውስጥ ካስገባች እና ገንዘቧ ዓለማቀፍ ተቀባይነት አግኝቶ ሃገራት ሊተውት በማይቻል መጠን በብዛት ካከማቹት በኋላ ፊቷን በማዞሯ ምክንያት ለአጭር ጊዜ ጥቅም በዘላቂነት ጥገኛ ለመሆን ተገደዱ። አሜሪካ በብሪቶን ውድስ ስምምነት መሰረት ዶላር እየመለሱላት  ወርቅ ሲቀበሏት የነበሩትን ሃገራት ሁሉ እስከዛሬ ድረስ በተቃራኒው ለዶላር ወርቅ እንድትከፍላቸው ማድረግ ችላለች። ይህ የሆነበት ምክንያትም ሃገራት የውጭ ምንዛሬ ክምችት የሚያስቀምጡት በዶላር አሊያም ደግሞ በወርቅ በመሆኑ ነው። ሃገራቱ ወርቃቸውን የሚሸጡበት ወይም በዶላር የሚቀይሩበት ዋጋ የሚተመነው በኒውዮርክ፣ለንደን እና ፓሪስ በሚገኙ ዓለማቀፍ የወርቅ ገበያዎች ነው። የዓለም  ሃገራት የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ክምችት 69በመቶው በአሜሪካ ዶላር የተቀመጠ ነው። ይህ ጽሁፍ በአጠቃላይ በአንድ ሃገር ላይ የሚደማመጡ ምሁራን፣ፖሊሲ አውጭዎች፣ሃሳብ አፍላቂዎች እና የፖለቲከኞች ጥምረት ሊታመን የማይችል ተዓምር መስራት እንደሚችል ማሳያ ይሆናል ባይ ነኝ።

ወርቅ፣ዶላር እና አሜሪካ!

Screen Shot 2017-08-26 at 23.24.14.jpg

(©Kidus Mehalu) ወርቅ ድንበርና ዜግነት ሳይወስነው በመላው ዓለም ተፈላጊ መሆኑ፣ ፖለቲከኞች እንደ ወረቀት ገንዘብ በፈለጉ ጊዜ ስለማያጋሽቡት፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላል እና በተፈለገው መጠን መስራት የሚቻል መሆኑ፣ ለብዙ ጊዜ ቢቀመጥ የማይበላሽ እና ዋጋውን ጠብቆ መቆየት የሚችል መሆኑ፣እንዲሁም በቀላሉ የሚተጣጠፍ፣ ጠንካራ እና እንደ ወረቀት ገንዘብ በማቃጠል ፈፅሞ ማጥፋት የማይቻል መሆኑ እውነተኛ ገንዘብ አሰኝቶታል። ለአንደኛውን የዓለም ጦርነት ዝግጅት አውሮፓዊያኑ መንግስታት እንዳሻቸው ማጋሸብ የማይችሉትን ወርቅን ከዓለም ገበያ ዋጋ ውጭ በከፍተኛ ሁኔታ ማራከሳቸው ሰዎች የያዙትን ወርቅ በገንዘብ እንዲለውጡ ከማድረጉም በላይ ወርቅ አውጭዎችም ቆፋሮ እንዲያቆሙ አስገደዳቸው። ይህም ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ዋጋ መለኪያ የሆነው ወርቅ በሌሎች ሃገራት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ ሰዎች በወርቅ ላይ የነበራቸው እምነት መሳሳቱ እና ዓለማቀፍ የወርቅ አቅርቦት መገታቱ ከጦርነቱ በኋላ ዓለም ሲጠቀምበት የነበረው ወርቅን ማዕከል ያደረገው ግብይት ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ ምክንያት ሆነ። ወርቅን ማዕከል ያደረገው ዓለማቀፍ የገንዘብ ዋጋ ስሌት መቅረቱ የዓለምን የንግድ ሚዛን ከማዛባቱም ጋር ተዳምሮ በአሜሪካ ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት መከሰት ዓለም ከገባችበት ምስቅልቅል ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት በማጨናገፉ ምክንያት አውሮፓ ላይ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እሳት ሊነድ ግድ ሆነ።

አውሮፓዊያኑ በጀርመን አሳራቸውን በሚያዩበት ወቅት ዓለም አይታው በማታውቀም የኢኮኖሚ መቅሰፍት የተመቱት አሜሪካዊያን ከችግራቸው ለመላቀቅ ላይ ታች እያሉ ነው። እኤአ ታህሳስ 7ቀን 1941ዓ/ም የአሜሪካን ባህር ሃይል በጃፓን ጦር በድንገት መመታቷን ተከትሎ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ ህጋዊ ምክንያት አገኘች። አሜሪካ ከዳርእስከዳር “ጃፓንን እንበቀላለን!እንዋጋለን” በሚሉ ወዶዘማች አሜሪካዊያን ወጣቶች አመጽ ተናጠች።የአሜሪካ ኮንግረስ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የወጣውን እና አሜሪካ በሌላ ሃገር ጦርነት ውስጥ እንዳትሳተፍ የሚከለክለውን አዋጅ ተነሳ። ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት በጃፓን፣ ጀርመን እና ኢጣሊያ ላይ ልጓም ለማበጀት አሜሪካ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ መግባቷን በይፋ አወጁ።

የአሜሪካ የምጣኔ ሃብት ጠበብቶች፣የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሊቃውንቶች እና ሃሳብ አመንጭዎች በበኩላቸው ወርቅን ማዕከል ያደረገው የዓለም የንግድ እና የገንዘብ ግብይት መቅረትን ተከትሎ የተዛባውን የዓለም ንግድ ሚዛን ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዳ ውጥን ሲነድፉ፣ሲወያዩ፣ሲከራከሩ፣ሃሳብ ሲጨመሩ እና ሲቀነሱ ቆይተው በሐምሌ ወር 1944ዓ/ም አንድ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ። በኒው ሃምሻየር ግዛት ውስጥ ብሪቶን ውድስ በሚባል አካባቢ ለመረጧቸው 44 ሃገራት ያስተዋወቁት ይህ ፕሮጀክት ዓላማው ሃገራት የአሜሪካ ገንዘብ የሆነውን ዶላር እንደወርቅ ቆጥረው ቢያከማቹ እና ቢገበያዩበት በፈለጉ ጊዜ ዶላሩን እየተቀበለች በወርቅ የመለወጥ ግዴታ ሲሆን ሂሳቡ በቋሚነት የሚሰላውም የአንድ ወቄት ወርቅ(28.67ግራም ወርቅ) ዋጋ 35 ዶላር ሆኖ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ መጠነ ሰፊ የወርቅ እጥረት እንደሚያጋጥም ግልጽ ስለነበር በወቅቱ ዶላር እንደ አማራጭ መቅረቡ ሁሉም በደስታ ተቀበለው። ሆኖም ግን ያኔም ሆነ ዛሬ ዶላር ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ንግድ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት ስለሆነ አውሮፓዊያኑ ንግድን ማስፋፋት እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ ማበረታታት ተያያዙት። እኤአ እስከ 1950ዎቹ ድረስ ይህንን አጠናክረው በመቆየት የነበረባቸውን የዶላር ችግር ከማስወገዳቸውም በተጨማሪ የንግድና ኢንቨስትመንቱ መቀጠል የዶላር ክምችታቸው በጣም ከፍ እንዲልም ረድቷቸዋል። የአሜሪካ ዶላር ተቀባይነትም በመላው ዓለም በመስፋፋቱ  ዓለም ዓቀፍ ገንዘብ ሆኖ ሲሰራ የነበረውን ወርቅ ሙሉ ለሙሉ የአሜሪካ ዶላር ተካው። በ1960ዎቹ የአሜሪካ ዶላር ዓለምን አጥለቀለቀ።

ሆኖም ግን የብሪቶን ውድስ ስምምነት ዓለምን ወርቅን ማዕከል(ጎልድ ስታንዳርድ) ካደረገው የግብይት ስርዓት ዶላርን ማዕከል(ዶላር ስታንዳርድ) ወዳደረገው ስርዓት በይፋ ቢያሸጋግርም ከዚህ በኋላ ዶላርን ለሌሎች ሃገራት በወርቅ መለወጥ ‘ጅልነት’ መሆኑን የአሜሪካ ምሁራን መናገር ጀምሩ። ምክንያቱም የወረቀት ገንዘቦችን ለመስራት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች እና የህትመት ወጭ አንድ ግራም ወርቅን ከመሬት ቆፍሮ ከማውጣት ጀምሮ ለገበያ እስከማቅረብ ድረስ ካለው ወጭ አንጻር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል እያንዳንዱን ባለ 1፣ ባለ 5፣ ባለ20፣ ባለ 50 እና ባለ 100 የአሜሪካ ዶላር ለመስራት 75% ጥጥ እና 25%ላይሎን ጥቅም ላይ ይውላል። የሁሉም ክብደት 1 ግራም አካባቢ ሲሆን እያንዳንዱን ዶላር ለማምረት የሚወጣው የገንዘብ ወጭ 4 የአሜሪካ ሳንቲም ብቻ ነው። እንግዲህ አስቡት በብሪቶን ውድስ ስምምነት መሰረት ሃገራት ያከማቹትን ዶላር ለአሜሪካ እየሰጡ በምትኩ ወርቅ ይቀበላሉ። ይህም ማለት ለምሳሌ 35 ዶላር ለሚያመጣ ሃገር 28.67 ግራም ወርቅ ትከፍላለች ማለት ነው። የምሁራኑ የጩኸት ምንጭም ይሄው ነው። 35የአሜሪካ ዶላር ለማተም ለምሳሌ (ባለ 1 ዶላር) ወጭው 1.4 ዶላር ነው።35ቱ ዶላር ባለ20፣10 እና 5 ዶላር ተደርጎ ቢከፈል ደግሞ ወጭው 0.12ዶላር ነው። ይህን ያክል ወጭ ለሚፈጅ ዶላር 28.67 ግራም ወርቅ መክፈል የእውነትም ዘላቂ ሊሆን አይችልም። እኤአ ነሃሴ 15 ቀን 1971 ዓ/ም ከገንዘብ ሚንስትራቸው ጆን ኮናሊ፣ የብሄራዊ ባንኩ ሊቀመንበር አርተር በርንስ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው ሄርበርት ስቴይን እና ፖል ቮከር ጋር ሆነው ካምፕ ዴቪድ ውስጥ በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ ዋሉ።  •••(ይቀጥላል)